15/10/2026
እውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ ውድ ነውን?
“ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው” መዝ. 119፥ 105
-
BSE ጥቅምት 05, 2019 ዓ.ም
+++++++++++++
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በተለይ በዘመናችን መጽሐፍ ቅዱስን አስተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ምን ያህል አዳጋች እየሆነ እንደመጣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ሆኖም አልፎ አልፎ በመረጃ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች አሁን ያለውን አሳሳቢ ችግር ያለመረዳት ሁኔታ ስለሚታይ፤ ይህችን ጽሑፍ ለማጋራት ወደናል። ጽሑፍ ትንሽ እረዘም ያለ ቢሆንም እጅግ ጠቃሚ እና ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ በትዕግሥት እንድታነቡት በትህትና እንጠይቃለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በውጭ ሀገር ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የሚከፈሉ ክፍያዎች እና ወጪዎች :-
እርግጥ ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ በገንዘብ የሚለካ እና የሚመዘን አይደለም። ሆኖም አገልግሎቱ እንዲጠናከርና እንዲሰፋፋ የግድ ገንዘብ ያስፈልጋል። የዚህ ጽሑፍና መረጃ ዓላማም በሀገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን አሳትሞ ለማዳረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመሳል? የሚለውን ለማሳይተና ግንዛቤ ለመፈጠር ነው። ብሎም ሁላችንም ለዚህ አገልግሎት ኃላፊነት እንዳለብን ለማጠየቅ ነው።
ከዚህ በፊት እንደገለጽነው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በውጭ ሀገር የሚያሳትማቸውን በርካታ መጽሐፍ ቅዱሶች የሕትመት ሥራቸውን የሚከናወነው በቻይና እና በኮሪያ ነው። በዚህ ምክንያት ወጪው እጅግ ከፍተኛ ነው። ለአብነት መጽሐፍ ቅዱሱ በውጪ ሀገር ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ሕትመቱን ሳይጨመር የሚኖሩት ወጪዎች እንመልከት፦
• የጉምሩክ ቀረጥ ክፍያ
• የመርከብ ማስጫኛ፥ ማጓጓዣና ኢንሹራንስ
· የወደብ መጋዘን ኪራይ ክፍያ
· በጉምሩክ ቆይታ የሚከፈሉ ክፍያዎች (የመጋዘን ኪራይ እና ሌሎች ተዛማጅ ክፍያዎች)
· ከጅቡቲ አዲስ አበባ የትራንስፖርት ክፍያ
· ለጉምሩክ አስተላላፊዎች የአገልግሎት ክፍያ
· የማስጫኛና ማውረጃ ክፍያ
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ወጪዎች እንግዲህ የትርጉም እና የሕትመት ወጪዎችን ሳይጨምር ነው። ነገር ግን ማኅበሩ ለትርፍ ያልተቋቋመ በመሆኑ ሕትመቱን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩትን ወጭዎች አውጥቶ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባውን መጽሐፍ ቅዱስ ተደራሽ ለማድረግ ከ15% እስከ 20% የዋጋ ድጎማ (Subsidy) ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ ምንም መግዛት አቅም ለሌላቸው ወገኖች፥ ለማርሚያ ቤቶች፥ ለስደተኛ ጣብያዎች፥ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት እና ለመሳሰሉት ደግሞ በነጻ ያሰራጫል።
አንዳንድ ወገኖች በአሁኑ ጊዜ ማኅበሩ መጽሐፍ ቅድስ የሚሠራጭበት ዋጋ በጣም ውድ ነው ሲሉ ይሰማሉ:: እውነት ነው በተለይ በጣም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖቻችንን ስንመለከት ዋጋው ከፍተኛ ሊሆንባቸው ይችላል። ነገር ግን ይህንን አባባል በመጠኑ የተሻለ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ሲናገረው መስማት ይከብዳል። ብዙዎቻችን ለተለያዩ ልብ ወለድ መጻሕፍትና መጽሔቶች ቀላል የማይባል ዋጋ ከፍለን ለማንበብ ብዙ ሳንቸገር፥ ለሁለት ወይንም ለሦስት ለማክያቶ የምናወጣው ወጪ (እነዚህ የተጠቀሱት አይስፈልጉም ማለት አይደለም) ሳይከብደን ወይንም ሳናማርርበት ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ተዘጋጅቶ (ያውም የሕትመትና ልዩ ልዩ ወጪዎቹ 98% በውጪ ድጋፍ በተሸፈነ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ) ከወጣበትም አጠቃላይ ወጪ ድጎማም ተደርጎበት የሚተመነው የማሰራጫ ዋጋ ሲከበደንና ስናማርር ይታያል።
ዛሬ በነዳጅ ዋጋ መጨመር የትራንስፖርት ዋጋ ለውጥ እንዳለው ግልጽ ሆኖ ሳለ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ የሚደረግ እጅግ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ጥያቄ ሊያስነሳ ይገባልን? ለመሆኑ በጥቂት ወራት ውስጥ እንኳን በተለያዩ ከውጪ ሀገር በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ መጠን በመጽሐፍ ቅድስ ላይ ጎልቶ ታይቶአልን? ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ መወደዱ፤ ብሎም በተፈለገው ጊዜና ቦታ አለመገኘቱ ብዙዎችን ያሳስባል፤ ይህ እጅግ ተገቢ ስጋት ነው። ሆኖም ሰንቶቻችን ለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ የመፍትሔው አካል ለመሆንና አስተዋጽኦ ለማድረግ አራሳችንን አዘጋጅተናል? አነዚህን ጥያቄዎች ሁላችንም ልናጤናቸው ብሎም የአገልግሎቱን ከባድነት ሊያሳዩን ይገባል።
በመጨረሻ
* የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከላይ በተዘረዘረው ሁኔታ ብዙ ሚሊዮን ብር የሚጠይቀውን ይህን ተግባር ለማከናወን የበጀት ድጋፍ ከየት ያገኛል?
* በሀገር ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ለሥራው ምን ያህል የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው?
* በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የመጽሐፍ ቅዱስ እጥረት ለምን ተከሰተ መፍትሔውስ ምንድነው?
* ማኅበሩስ ችግሩን መናገር ብቻ ነው ወይንስ የመፍትሄ እስታራቴጂ ነድፏል?
የሚለውን በሚቀጥለው እንመልስበታለን።
ይቆየን!